WEDP

25 December 2019 ሻሂዳ ሁሴን

የሴቶች ኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ፕሮጀክት በፌዴራል ከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ሥር ከሚገኙ ፕሮግራሞች አንዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥትና በዓለም ባንክ ትብብር ይፋ የተደረገው እ.ኤ.አ. በ2012 ሲሆን በንግድ፣ በአገልግሎትና በምርት ሥራ ለተሰማሩ ሴቶች የሥልጠናና የብድር አገልግሎት የመስጠት ተልዕኮ አለው፡፡  

ሲጀመር የአምስት ዓመት ፕሮግራም የነበረ ሲሆን፣ ውጤታማነቱ ታይቶ ተጨማሪ የሁለት ዓመታት ጊዜ የተሰጠው እ.ኤ.አ. በ2017 ነበር፡፡ የተራዘመለት ጊዜ በመጠናቀቁ ሌላ ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድለት ዳግመኛ ጥያቄ ቀርቧል፡፡ በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱ መቐለ፣ ባህር ዳር፣ አዲስ አበባ፣ ዲላ፣ አሰላ፣ አዳማ፣ ሐዋሳና ጎንደርን ጨምሮ በአሥር ከተሞች እንደሚተገበር የሚናገሩት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ሰለሞን፣ በመጀመርያዎቹ የፕሮጀክቱ መተግበሪያ ጊዜያት የአገልግሎቱ ተደራሽነት በስድስት ከተሞች ላይ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ. በ2019 መጨረሻ ላይ የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ የተጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ ከተፈቀደ አገልግሎቱ የሚሰጥባቸው ከተሞች ቁጥር ወደ 18 አሳድጎ ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል፡፡

በፕሮጀክቱ የሚሰጡ ሥልጠናዎች የሥራ ፈጠራና የሙያ በሚል ለሁለት የተከፈሉ ናቸው፡፡ በምርትና በአገልግሎት ሥራ የተሰማሩ ሴቶች የሙያ ሥልጠና ሲወስዱ፣ በምግብ ዝግጅት፣ በልብስ ስፌት፣ በቆዳ ሥራና በመሳሰሉት በተሰማሩባቸው የሥራ መስኮች ውጤታማ የሚያደርጋቸውን ሥልጠና እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ ገበያቸውን፣ ደንበኞቻቸውን እንዲያውቁ አቅደው መሥራት እንዲችሉም የሥራ ፈጠራ ሥልጠና ይሰጣቸዋል፡፡

በዚህ ሥልጠና የተሳተፉ በተሰማሩባቸው የንግድ ዘርፎች የተሻለ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡ ችግሩ ሥልጠናው እንደሚያስፈልጋቸው አሳምኖ እንዲጀምሩ ማድረጉ ላይ ነው፡፡ ሴቶቹ በተለያዩ ኃላፊነቶች የተጠመዱ ከመሆናቸው አንፃር ለሥልጠና ጊዜ መስጠት እንደ ድሎት፣ እንደ ቅብጠት ይቆጠራል፡፡ 

‹‹ጥቅሙን አይገነዘቡትም፡፡ ጊዜ እንደ ማጥፋት ነው የሚቆጥሩት፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሴቶች ራሳቸው አስተዳደሪ፣ ራሳቸው ሻጭ፣ ራሳቸው አምራች ናቸው፡፡ የቤተሰብም ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ጊዜያቸውን ማባከን አይፈልጉም፤›› በማለት አቶ ዮሐንስ ሴቶችን ወደ ሥልጠና በማምጣት ረገድ ያለውን ችግር ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ለ20,569 ሴቶች የሥራ ፈጠራና የሙያ ሥልጠና መስጠት ችሏል፡፡ ከሥልጠና ባሻገር ፕሮጀክቱ የሚያመቻቸው የብድር አገልግሎት በሺዎች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች እንዲወጡ እያደረገ ነው፡፡ እስካሁን 13,312 ሴቶች 3.6 ቢሊዮን ብር ብድር ማግኘት ችለዋል፡፡ ‹‹ብድር አሰጣጡና አመላለሱ ፕሮጀክቱ ውጤታማ እንዲሆን ካደረጉ ነገሮች ዋነኛው ነው፤›› ያሉት አቶ ዮሐንስ፣ 98.4 በመቶው ብድር ወቅቱን ጠብቆ ለአበዳሪዎች እንደሚመለስ ገልጸዋል፡፡

ደንበኞች ለንግድ ማስፋፊያ የሚሆናቸውን የገንዘብ ብድር የሚያገኙበት የተለየ ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ ለፕሮጀክቱ መጀመር እርሾ የሆነው ከዓለም ባንክ የተገኘው 50 ሚሊዮን ዶላር የብድር ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንዲገባ ተደረገ፡፡ ገንዘቡ እንዴትና በምን ዓይነት መልኩ ለተጠቃሚዎች እንደሚደርስና ከምን ዓይነት አበዳሪ ተቋማት ጋርም በትብብር እንደሚሠራ ልማት ባንክ ከዓለም ባንክ ጋር በመስማማት ያወጣው መሥፈርት አለ፡፡ መሥፈርቱን የሚያሟሉ የአነስተኛ አበዳሪ ተቋማት ከፕሮጀክቱ ጋር ተቀናጅተው እንዲሠሩ ይደረጋል፡፡ በዚህ መሠረት 12 አነስተኛ አበዳሪ ተቋማት ተመርጠው በጋራ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አበዳሪ ተቋማት የሚያበድሩትን ገንዘብ ከልማት ባንክ በውል ይወስዳሉ፡፡ የሚወስዱት ገንዘብ እንደ አቅማቸው የሚለያይ ሲሆን፣ በጨረሱ መጠን ሪፖርት እያቀረቡ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡

በዚህ ሥርዓት የሚመራው የብድር አገልግሎት ከ13 ሺሕ የሚበልጡ ሰዎች ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል፡፡ ተበዳሪዎች በአግባቡ ብድር መመለሳቸው አበዳሪ ተቋማቱ በሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲጥሉ ማድረጉን የሚናገሩት አስተባባሪው፣ ከልማት ባንክ የሚለቀቅላቸው ብድር ሲዘገይ ተቋማቱ ከራሳቸው ቋት ሳይቀር እያወጡ እንደሚያበድሩ ያስረዳሉ፡፡ በፕሮጅክቱ ለብድር ከዋለው 3.6 ቢሊዮን ብር ውስጥም 27 በመቶ የሚሆነው የተቋማቱ ድርሻ እንደሆነ አቶ ሰለሞን ያስረዳሉ፡፡

ይህ ፕሮጀክት ይፋ እንዲሆን በመጀመርያው የብድር ዘመን ዓለም ባንክ 50 ሚሊዮን ዶላር፣ ቀጥሎ የጣሊያን መንግሥት 15 ሚሊዮን ዩሮ፣ የጃፓን መንግሥት 50 ሚሊዮን ዶላር ብድር ሰጥተዋል፡፡ የፕሮጀክቱ ዕድሜ በድጋሚ ከተራዘመ ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት የሚሆን ከአውሮፓ ኅብረት የተገኘ 30 ሚሊዮን ዩሮ ገንዘብ አለ ብለዋል፡፡  

ፕሮጀክቱ በየዓመቱ 1.1 ቢሊዮን ብር የማበደር አቅም እንዲኖረው እየሠራ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለተገልጋዮች የሚያበድረው ገንዘብ መጠን 117 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ገንዘቡ እየተገላበጠ ተመልሶ ለብድር እንዲውል መፈቀዱ ለፕሮጀክቱ ቀጣይነት ደጀን ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት 35,604 ሴቶች አገልግሎቱን ለማግኘት ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ የፕሮጀክቱ ሁለተኛ ምዕራፍ ተጠንቶ እንዲቀጥል የዓለም ባንክ ፍላጎት ማሳየቱን አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡

በብድሩ ተጠቃሚ የሆኑ ሴቶች ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በሚያዘጋጃቸው ዕድሎች የሚጠቀሙ ሴቶች ከ100 ሺሕ እስከ 500 ሺሕ ብር ድረስ በአንዴ በብድር መልክ እየወሰዱ የሚጠቀሙና የብድር ፍላጎታቸውም እያደገ የሚመጣ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሚሊዮኖች ብድር የሚጠይቁ ደንበኞችን መፍጠር ተችሏል፡፡

ይሁንና የአበዳሪ ተቋማቱ አቅም አይፈቅድምና ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ለሚፈልጉ ደንበኞች አጥጋቢ ምላሽ መስጠት ከባድ ነው፡፡ እስካሁን የብድር አገልግሎት ማግኘት ከቻሉት 13,312 ሴቶች መካከል ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ያገኙ 150ዎቹ ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የመበደር አቅም ያላቸው  ደንበኞችን ወደ መደበኛ ባንኮች ማስተላለፍ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ምክክር እየተደረገ መሆኑን አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡

ሥልጠና ከመስጠትና የገንዘብ ድጋፍ ከማመቻቸት ባሻገር ፕሮጀክቱ የተለያዩ ማሽነሪዎችን ማግኘት ለሚፈልጉ ነጋዴና ሥራ ፈጣሪ ሴቶች በሊዝ መግዛት የሚችሉበትን የመግባቢያ ሰነድ በዘርፉ ከተሰማሩ ተቋማት ጋር ተፈራርመዋል፡፡ በፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ፣ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል ካፒታልና ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ሥራ አክሲዮን ማኅበራት መካከል ነው ታኅሣሥ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ስምምነቱ የተደረገው፡፡ 

By admin

Leave a Reply

Your email address will not be published.